Ethiopia,sudan and egypt signed agreement over nile water sharing

ኢትዮጵያና ግብፅ በዳግም ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ላይ ናቸው?

August 29, 2017 99 1 No Comments

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ግንኙነት በማንኛውም መሥፈርት እጅግ የተወሳሰበ ነው፡፡ ለዘመናት በእርስ በርስ ጦርነት፣ ግጭትና ፖለቲካ ፍትጊያ ውስጥ አልፈዋል፡፡ አልፎ አልፎም ሁለት ሆነው በማበር አንዱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ያሴሩበት አጋጣሚም ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጥምረቶች በተለያዩ ዓውዶች ውስጥ ሲለዋወጡም ተስተውሏል፡፡ ይሁንና የግብፅና የሱዳን ጥምረት ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ላይ በርካታ ጉዳቶችን አስከትሏል፡፡ ከዚህ እውነት በተቃራኒ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሱዳን ቀስ በቀስ ከግብፅ እየራቀችና ወደ ኢትዮጵያ እየቀረበች በመምጣቷ፣ አንዳንዶች አዲስ ጥምረት በቅርቡ ሊታይ እንደሚችል መገመት ጀምረዋል፡፡

በናይል ጉዳይ ላይ የሚሠሩ የፖለቲካ ተንታኞች ይህ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ያለባትን ዲፕሎማሲያዊ ጦርነት በድል ለመወጣት የተለየ ታክቲክ እንድትጠቀም እንዳስገደዳት ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም ከተፋሰሱ አገሮች መካከል አዲስ አጋር ለማግኘት በመኳተን ላይ ትገኛለች፡፡ የግብፅ ፕሬዚዳንትም ወደ እነዚህ አገሮች ሲመላለሱ ማየት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡

ይኼው አዝማሚያ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በቅርቡ ወደ ሩዋንዳና ታንዛኒያ ባደረጉት ጉብኝት ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን ጉብኝቱ ከተደረገበት ጊዜና ቦታ አንፃር ይህን ጉብኝት የተለመደ ነው ብሎ ማለፍ አይቻልም፡፡ ሩዋንዳና ታንዛኒያ ከኢትዮጵያ ጋር በመሆን የናይል ቤዚን ሁሉን አቀፍ የትብብር ማዕቀፍ (ሲኤፍኤ) ያፀደቁ ብቸኛ አገሮች ናቸው፡፡ ጉብኝቱ የተደረገበት ጊዜም ቢሆን የግብፅን ሥሌት ያሳያል፡፡ ከሁለት ወራት በፊት በካምፓላ ኡጋንዳ በዩዌሪ ሙሴቬኒ ግብዣ የተፋሰሱ አገሮች መሪዎች በተገናኙበት ወቅት፣ ግብፅ በቅድመ ሁኔታ ታጅባ ወደ ናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ (ኤንቢአይ) ለመመለስ ጥያቄ አቅርባ ነበር፡፡ ቅድመ ሁኔታዋ በሲኤፍኤው አንቀጽ 14 (ቢ) ላይ እንዲካተት ከምትፈልገው የውኃ ደኅንነት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ አዲስ ሲኤፍኤ እንዲረቀቅ ሐሳብ ያቀረበችው ግብፅ በናይል ውኃ ላይ የአንበሳውን ድርሻ የሚሰጣት በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረመው ስምምነት የዚሁ አካል እንዲሆን ጠይቃለች፡፡ አብዛኞቹ አገሮች ግብፅ ኤንቢአይን በድጋሚ ለመቀላቀል ፍላጎት ማሳየቷን ያበረታቱ ቢሆንም ቅድመ ሁኔታዋን አልተቀበሉትም፡፡

ከተፋሰሱ አገሮች በተለይ ኢትዮጵያ የግብፅን ቅድመ ሁኔታ አምርራ ተቃውማለች፡፡ ኢትዮጵያ ሲኤፍኤው ላይ ክርክርና ድርድር ተደርጎ ካበቃ በኋላ ስምምነቱ ለማፅደቅ ክፍት ተደርጎ ሦስት አገሮች በፓርላማቸው አፅድቀውት እያለ፣ በድጋሚ ለድርድር ክፍት የሚሆንበት ምክንያት እንደሌለ አስረድታለች፡፡ ግብፅ በድጋሚ የኤንቢአይ አባል ለመሆን የምታቀርበው ሐሳብ ላይ በቅርቡ የሚካሄደው የናይል ቤዚን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በዝርዝር ለመነጋገር  ቀጠሮ መያዙን ከኤንቢአይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ የአልሲሲ ጉብኝትም በዚሁ ጉዳይ ላይ ለተሳታፊዎቹ ቅድመ ገለጻ በማድረግ ላይ ያነጣጠረ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

የአልሲሲ ጉብኝት ቻድና ጋቦንን ጨምሮ አራት የአፍሪካ አገሮችን ያካለለ ሲሆን፣ በሩዋንዳና በታንዛኒያ በነበራቸው ቆይታ ወቅት አዲሱን የግብፅ ሐሳብ በማብራራት ለማሳመን መጣራቸው ሚስጥር አልነበረም፡፡ እንደተለመደው እ.ኤ.አ. በ1959 ከሱዳን ጋር የፈረሙትን ስምምነት በመጥቀስ ከናይል ውኃ ዓመታዊ ድርሻቸው 55.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ላይ መቀነስ የሚታሰብ እንዳልሆነ አሳስበዋል፡፡ አልሲሲ የግብፅን ሥጋት “የሕይወትና የሞት ጉዳይ” ሲሉ ገልጸውታል፡፡

የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊና የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ የግብፅን ሥጋትና ፍላጎት እንደሚገነዘቡ ቢናገሩም፣ ከሲኤፍኤው ወደ ኋላ የማለት አዝማሚያ አላሳዩም፡፡ ሁለቱም መሪዎች ለናይል ውኃ ችግሮች ሁሉም አባል አገሮችን ያቀፈ መፍትሔ መስጠት እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወደ ሱዳን በማቅናት ለሦስት ቀናት ይፋዊ  ጉብኝት ያደረጉት፣ በተመሳሳይ ሳምንት መሆኑ የአጋጣሚ ጉዳይ አይመስልም፡፡ እርግጥ ነው የኢትዮጵያ መንግሥት ከግብፅ በተቃራኒ ይህ ጉብኝት የፖለቲካ ግብ እንደሌለው ገልጿል፡፡ በተለይ ከናይል ውኃ ጋር የተያያዘ ልዩ የውይይት አጀንዳ እንዳልነበረ አስታውቋል፡፡ ሁለቱ አገሮች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሁለትዮሽ ስምምነት ማድረጋቸውም ተመልክቷል፡፡ ይሁንና በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ጉብኝት ከናይል ውኃ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያምናሉ፡፡

ሁለቱ አገሮች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንዳደረጉ የተገለጸ ቢሆንም፣ ኤንቢአይና ዋነኛ ዓላማው የሆነውን ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍልን ዕውን ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆኑ መናገራቸው የመገናኛ ብዙኃኑን ትኩረት ስቧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር በሰላምና ደኅንነት፣ በኢኮኖሚያዊ ትስስር፣ በድንበር ጉዳዮችና በመሳሰሉት ላይ መነጋገራቸውም ተገልጿል::

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጉብኝት ዓላማ እንደ ፕሬዚዳንት አልሲሲ በግልጽ ከናይል ውኃ ዲፕሎማሲ ጋር የተገናኘ ነው ለማለት አዳጋች ቢሆንም፣ ኢትዮጵያና ግብፅ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ ዳግም ስለመግባታቸው ግን ከበቂ በላይ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ ውጥረት አንፃር የሲኤፍኤው ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ብሎ መጠየቅም ምክንያታዊ ነው፡፡

NEWS