ዶ/ር መረራ ጉዲናከ እስር ተለቀቁ

ዶ/ር መረራ ጉዲና ከእስር ተለቀቁ

January 17, 2018 437 17 No Comments

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ዛሬ ከእስር ሲፈቱ “ከ400 ቀናት በኋላ በሰላም ከእስር በመለቀቄ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። እንምታየው ሰዎች በድምቀት ተቀብለውኛል” ሲሉ ለቢቢሲው ኢማኑኤል ኢጉንዛ ተናግረዋል።

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚንስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ለቢቢሲ ”ዶ/ር መረራ ነጸ ወጥተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዶ/ር መረራ ጉዲና ዛሬ ከእስር ሊፈቱ እንደሚችሉ የማረሚያ ቤት ሃላፊዎች ነግረውናል ሲሉ የዶ/ር መረራ ቤተሰብ አባላት ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የቤተሰብ አባላቱ ጨምረውም እንደተናገሩት ዛሬ ጠዋት ዶ/ር መረራን ለመቀበል የቤተሰብ አባላት እና ወዳጆቻቸው ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቅንተው የነበረ ሲሆን፤ የማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎች ዶክተር መረራን ራሳቸው አሸዋ ሜዳ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እንደሚወስዷቸው በመግለጽ እዚያው እንዲጠብቁ ነግረዋቸዋል።

ደጋፊዎቹም መልዕክት የያዙ ጽሑፎችን በመያዝ እና የዶ/ር መረራ ምስል የታተመበትን ቲሸርት በመልበስ በቤታቸው አቅራቢያ እየጠበቋቸው ይገኛሉ።

በ2008 ዓ.ም በተለይ በኦሮሚያና በአማራ አካባቢዎች ተቀስቅሶ ለወራት የዘለቀውን ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመተላለፍ ”ከፀረ-ሠላም” እና ”ከሽብር” ቡድኖች ጋር ግንኙነት በማድረግ ለእስር መዳረጋቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ዶክትር መረራ በፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪነታቸውና በተቃዋሚ ፓርቲ መሪነት ለዓመታት ባካበቱት እውቀትና ልምድ ስለኢትዮጵያ የተለያዩ ፅሁፎችንና ንግግሮችን እንዲያቀርቡ በተለያዩ መድረኮች በአስረጂነት ይጋበዛሉ።

ከነዚህም መካከል እስር ቤት ከመግባታቸው ቀደም ብሎ ጥቅምት 30/2009 ዓ.ም በአውሮፓ ፓርላማ ተገኝተው በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ ባደረጉት ንግግር በመንግሥት የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተችተው ነበረ።

በተጨማሪም በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጩ ምስሎች ላይ በሃገሪቱ ፓርላማ አሸባሪ ድርጅት ተብሎ የተፈረጀው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን መሪ ከሆኑት ዶክትር ብርሃኑ ነጋ ጎን ተቀምጠው መታየታቸውን አንዳንዶች ለእስራቸው እንደተጨማሪ ምክንያት ያነሳሉ።

 

 

NEWS